የእኛ የኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት፣ 2018፣ በደጅ ነው። አዲሱን ዓመት እንዴት እንቀበለው? 2018ን ስናስብ ከሚሰማን እንጀመር። ለአፍታ ያህል ሀሳባችንን ተወት አድርገን አካላችንን ለማድመጥ እንሞክር። አካላችን ምን ሹክ አለን? ሰውነታችን ውጥር ጥብብ ሲል ተሰማን ወይስ ተፍታታ?
አብይ የሆኑ አመለካከቶች
አዲሱ ዓመት አጠባበቅ ተቃርኖ ሊባሉ የሚችሉ ሁለት ዕይታዎችን ይንጸባረቁበታል። የመጀመሪያው የሚመጣው ዓመት በጎ ይጎላበታል ባይና እየጨመረ የሚሄድ ንጋትን ጠባቂ ነው። ነገ የበለጠ ይሠምራል ብሎም ያምናል። የከበበን የዛሬው የፍትህ መታጣት፣ ሌብነት፣ መገፋፋት፣ የከበበን ሥጋት፣ በልማት ስም የሚፈናቀሉ ሰዎች እንባ፣ በየቀኑ የሚፈሰው የንጹሀን ደምስ ሲባል መልሱ እኚህ ሁሉ በነገው በጎነት ይሸነፋሉ ነው። አተያዩ የዛሬ ክፋት ከነገ ጋር ስላለው ትሥሥር አምብዛም አይጨነቅም፤ “ድንገቴ በረከት” ጠባቂነት ይጎላበታል። የድንገቴ በረከት አጠባበቁም በተቺዎቹ መንገዱን የተላሎች ወይም የየዋሆች ተብሎ እንዲፈረጅ ያደርገዋል።
ሁለተኛው አጠባበቅ ክፋት ነገ ላይ ከዛሬ ይልቅ ይበልጥ እንደሚጨምር ይጠብቃል፤ ጨለማው ይበረታል የሚል ድምጸት ይጎላበታል። ሌሎች የሚጠቅሱዋቸው የመንገዶች ስፋት፣ በየመንገዱ እና በየለሊቱ ብቻውን የሚንቦገበገው ብርሃን፣ በየጊዜው የሚመረቁት እና የሚጀመሩት የብዙ ቢሊዬኖች ፕሮጀክቶች ዐይኖቻቸው አይገቡላቸውም። እኚህ ሁሉ መሠረተ ልማቶች ከሰው ልማት አንጻር እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም ብለው ይተቹዋቸዋል። ስለ ክፋት መጨመርም መረጃ ብቻ ሳይሆን ማስረጃዎቹን ሰንደዋል፣ በብዙ መልኩ የተጀመረው የአዝቅት ጉዞ ይበልጥ አቆልቁሎ ይታያቸዋል። አተያዩም በአዎንታውያኑ ጨለምተኛ በሚል ይፈረጃል።
የዚህ አሰላስሎ አላማ እነዚህን አተያዮች ማስታረቅ፣ መሞገት፣ ወይም ማሞገስ አይደለም። ጥያቄው ከነዚህ ሁለት ገዢ ቅኝቶች የሚሻል ሌላ አማራጭ አለን ነው። ክፋትን ሳይክዱና የእኛን አድራጊነት ሳያንኳስሱ ተስፋ ማድረግ ይቻላል የሚለውን ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ በእግዚአብሔር የምናምን እና ከዚሁ እምነታችንም የተለየ ጥንካሬ እና አይበገሬነትን የምንቀናጅ ከሁለቱ ገዢ ቅኝቶች የተለየ አተያይ እና አኗኗርን መከተል እንችላለን? የአሰላስሎው ዓላማ ሕይወታችንን ሆነ የሚቀጥለውን ዓመት አጠባበቃችንን በብዙ ክህደት እና ተላላነት ታጅቧል ተብሎ ከሚከሰሰው ሆነ ምንም የተስፋ ፍንጣቂ መመልከት ከሚቸገረውና በጨለምተኝነት ከሚከሰሰው አስተሳሰብ በተሻለ መልኩ ልንቃኝበት የምንችለውን ሦሥተኛ አማራጭን ለመጠቆም ነው።
የጌታ ቅርብነት
ሦስተኛው የዘመን አጠባበቅ መንገድ የጌታን ቅርብነት በመገንዘብ እና በመለማመድ ላይ የተመሠረተ ነው። አተያዩ ምንም ነገር ከማሰቡ በፊት የጌታን ቅርብነት በማስታወስ ይጀምራል። በጌታ ቅርብነት መቃኘት ደግሞ ብዙ ነገርን ይለውጣል። የከበበንን ክፋት ሳንክድ በተስፋ መኖር እንድንችል ያግዘናል። ተስፋ ለማድረግ በሚል ግን ያለንበት ዓለም የማስጨነቁን ልክ አንክድም፤ የእኛንም ሚናም አናንኳስስም። የከበቡንን ማስጨነቆችንም ከሌሎች የበለጠ ተገንዝበንም ተስፋ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ሰላም ባጣ ዓለም እየኖርን ሰላማችንን መጠበቅ እንችላለን እንላለን። የሚታየው ክፋት ልባችንን እና ሀሳባችንን እንዲጎትትና ተስፋ ወደ መቁረጥ እንዲወስደንም አንፈቅም። እንዲህ ዓይነቱ መንገድ ግን ይቻላልን?
ለሦስተኛ አተያይ መነሾ የሚሆነን ምንባብም ፊሊጲሲዮስ 4፡6-7 ነው። ክፍሉ “ ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” ይለናል። ክፍሉ የሚቃረኑ በሚባሉ ሁለት ውጥረቶች የተያዘ ነው፤ ስለመጨነቅ እና ስለ ሰላም ያሳስበናል።
አንዳንድ የሕይወት ገጠመኞች በእርግጥም ክፉዎች ናቸው። ብቻችንን የቀረን ያክል እንዲሰማን ያደርጋሉ። ፍጥረቱን በቸርነቱ የሚያስገባ የሚያስወጣ አምላክ እኛን ከመግቦቱ ያጎደለን ስሜት ይፈጥሩብናል። በሕይወታችን ለዘመናት የተለማመድነውን በጎነት በጥርጥር እንድናይ የሆነው ግን ወደን አይደለም። የደረሰብን ክፉ ነገር ህልውናውን እንድንክድ ባያደርገንም እንኳን የሁሌውን የደግነት አብሮነቱን በመተማመን እንዳንጠብቅ ያደርገናል። እንደመዝሙረኛው “አምላኬ ለምን ተውኽኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኽቴ ቃል ሩቅ ነህ።” (መዝ 22፤1) ስንልም እንገኛለን። እግዚአብሔር እንደተወን ይሰማናል፤ ለአድነኝ ጥሪያችን ሩቅ ሆኖ ይታየናል።
ሰው ነንና ማናችንም የሚዘልቅ ብቸኝነትን አንወደውም እና ሁኔታዎች ገፍተው ያደረሱን የብቸኝነት ጊዜያት ይረብሹናል። ከብቸኝነቶች ሁሉ የከፋው የብቸኝነት ስሜት ደግሞ የሁሉ ረዳት የሆነው አምላክ ብቻችን እንደተወን ወይም በጠላትነት እንደተነሳብን ሲሰማን ነው። ይኽንን ስሜት መዝሙረኛው (51፤11) ሲያስተናግድ “ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።” ሲል ተማጥኗል። የእግዚአብሔርን ቅርብነት በሕይወቱ የተለማመደ ሰው ደግሞ ከፊቱ መጣልን አይፈልግም።
በአምላክ የመተው ስሜት ከአሉታዊ ስሜቶቹ ሁሉ እጅጉን የሚያስፈራው ነው። ስለዚህም በእምነት የተሞላ ጸሎት ነው ብለን ባንኮራበትም እንኳን ራሳችንን አበረታተን ተውከን ያልነውን አምላክን መልሰን አትራቅ እያልን እንማጠነዋለን። “ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ።” ብለን እንዲያድነን እንጠራዋለን (መዝ 22 11)። አምላክ ርቆናል የሚለውን ስሜትም በታገለን ቁጥርም “አንተ ግን አቤቱ ከእኔ አትራቅ፣ አንተ ጉልበቴ እኔን ለመርዳት ፍጠን” (ቁ.19) ብለንም እንጮኻለን። የሚያዋጣው መንገድ በእርግጥም ይኼኛው መንገድ ነው።
በውጥረት ውስጥ የጌታን ቅርብነት ማስታወስ
ስጋት ሲከበን እና ጭንቀት ሲቀርበን ምን እናስታውስ? የሚያስጨንቀንን ነገር ሳንተው ከመጠን በላይ ከመብሰልሰል እና ከስሜታዊ አሉታዊነት ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ? “አይቻልም” ብቻ ከሚሰብከን ስሜትስ እንዴት ነጻ እንወጣ? ሐዋርያው በነዚህ ውጥረቶች ውስጥ አንድ ነገር እንዳንዘነጋ ያሳስበናል፤ እርሱም የጌታ ቅርብነት ነው። በጭንቀት መሃል የጌታን ቅርብነት ለራሳችን ሁል ጊዜ ከማሳሰብ መዘናጋት የለብንም።
የጌታን ቅርብነት ማሰብ የጌታን አብሮነት እና ብቻችንን አለመሆናችንን መረዳት ነው። በሁሉ ነገር ውስጥ ከጌታ አብሮነት ጋር መሆናችንን መገንዘብ አዲስ ኃይል ያስታጥቀናል። ከምንም በፊት ሁኔታዎች እያጎሉብን ከሚሰማን የተጣለ እና የተተወ ስሜት መንግለው ያወጡናል። የሰራን ጌታ፣ የሚጠነቀቅልን እና የሚንከባከበን መሆኑንም ልብም እንላለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ያመንን ቀን በእርግጥም ምንም ነገር አያስፈራንም።
በእግዚአብሔር አብሮነት ውስጥ የተለምዶው ፍርሀት የመሸሹ ምክንያት ግልጽ ነው። ነቢዩ እንደሚል የእግዚአብሔር አብሮነት ፍርሃታችንን ያስጠንግጠዋል፣ ድንጋጤያችን በመረጋጋት ይቀይራል፣ ድካማችን ይታገዛል፤ በመደገፋችንም እንበረታለን። ጌታ ቅርብ ነው ማለት በእርግጥም “አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።” መባል ነው (ኢሳ 41፤10)። የእኛስ ምኞት በአምላክ መደገፍ አይደለምን?
የጌታን ቅርብነት ማወቅ ብቻችንን እንዳልሆንን እንዲሰማን ያደርጋል። የምንደገፍበት ትከሻ የማይሰበር ሸንበቆ መሆኑን ስለምናውቅም እንረጋጋለን።
የጌታን አብሮነት መለማመድ
የጌታ ቅርብነት የሚሰጠን ሌላኛው መተማመን የምናወራውን ነገር ጌታ እንደሚሰማን ማወቅ ነው። ስለዚህም ነገራችንን ሁሉ፣ አንዳችን ሳናስቀር፣ ፊቱ በዝርዝር እንድናቀርብ አቅም ይሰጠናል። ስንናገርም፣ የሚያስፈልገንን ስናሳውቅም፣ እየሰማን እንደሆነ እርግጠኞች እንሆናለን። በሌላ አነጋገር አምላክ ቅርባችን ነው ማለት አምላክ አለ ማለት ብቻ አይደለም አምላክ አለልኝም ማለት ነው። የአምላክን ቅርብነት አዕምሮአዊ እውቀት ብቻ ስላልሆነም ልባችንን በፊቱ እናፈሳለን። በጸሎት፣ በልመና እና በምስጋና ም በፊቱ ራሳችንን እናቀርባለን።አብሮነቱን ማወቅ ኑሮዋችን የሚያስጨንቀንን የማሳወቅ እንጂ የመሳቀቅ እንዳይሆን ያደርገዋል።
ለጌታ ማሳወቅ ማለት ግን አንዳንዶቻችን እንደምናስበው ጌታን ማዘዝ አይደለም። የጌታን ቅርብነት ማወቅ ሁሉን ነገር በፊቱ ማምጣት እና በተጨነቅንበት ነገረ ጉዳዩ ላይ መሪነቱን ለእርሱ መተው ነው። ሁሉን በሚችል እና በሚያውቅ አምላክ ፊት ተገኝቶ መሪውን ካልጨበጥኩ ማለትስ እንዴት ልክ ሊሆን ይችላል? ከእኛ በጎ ሀሳቦች ይልቅ የእርሱ ደካማ የሚመስሉ መንገዶችስ በብዙ እጥፍ አይሻሉምን? በእርግጥም ከሰው ጥበብ ይልቅ የአምላክ ሞኝነት እጅጉን ይጠበባል (1ኛ ቆሮ 1፡25)።
ጸሎት ጉዳዬን ማስፈጸሚያ ነው የሚለው የተንጋደደ አስተሳሰብ ካልተሰተካከልን ግን ከጸሎት ብዙ አናተርፍም። ጸሎት የምንፈልገውን ነገር ከምናገኝበት መሳሪያነት ይልቅ ተደጋፊነታችንን ማስታወሻ መሆኑን፤ ከመናገር ይልቅ ማድመጥ እነደሚሻና ማሸነፊያ ሳይሆን በፈቃዱ መሸነፊያ ቦታነቱን ከሁሉ በፊት መረዳት ይገባናል። ጸሎት ጥያቄያችንን እኛ በፈለግነው መልኩ ማስመለስ ሳይሆን አምላካችን ለእኛ ያለውን ፈቃድ መገንዘቢያና ለፈቃዱም ፀጋ መጎናጸፊያ መሆኑን እንረዳ። በጸሎት ውስጥ የማይነጥፈው አቅርቦቱ ፀጋ ነው፤ ጸጋውም ሁሌ አሸናፊዎች ያደርገናል፤ በሰው ስሌት ታንፋችኋል እየተባልንም አሸናፊ ከተባሉት ሁሉ የበለጥን አሸናፊዎች እንሆናለን።
በጸሎት ውስጥ የምናገኘው የጸጋው አቅርቦት ግን ከምናስበው እና ከምንጠብቀውም በመጠንም ሆነ በይዘት ሊለይ እንደሚችልም ማስታወስ ይበጀናል። በፊቱ በመቅረብ ውስጥ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ እንደምናገኝ የተሰጠን ዋስትና የለም። የምንፈልገውን ነገር ያላገኘነውም አምላካችን ንፉግ ስለሆነ አይደለም። የፈለግነውን ነገር ያጣነው ከአምላክ ንፉግነት አንጻር ቢሆንማ ኖሮ በምናልፍበት ነገር ውስጥ የሚያስፈልገንን ጸጋንም ባላገኘንም ነበር::
በነውጥ መካከል ከበጎነቱ እንካችሁ ተብለን የተሰጠን ሰላማችንም የተደገፍነው ጌታ የሚረዳ እና የሚያግዝ ደግሞም ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገንን ከእኛ በላይ የሚያውቅ መሆኑን ከመረዳት ይመነጫል። የእግዚአብሔር ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ልባችንን እና አሳባችንን ይጠብቃል። በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የምናገኘው የሰላም ዓይነት አዕምሮን የሚያልፍ ነው።
አእምሮን የሚያልፍ ሰላም
በአብሮነቱ ውስጥ የምንቀዳው ሰላም ለምን አእምሮን የሚያልፍ ተባለ? አእምሮን የሚያልፍ ሰላም መገለጫው ምንድን ነው? አእምሮን የሚያልፍ ያሰኘው የእኛ የእጅ ሥራ አለመሆኑ ነው። ሰላሙ የምንቀበለው እንጂ የምንሠራው አይደለም። ለዚህም ነው መቋጫው መታበይና መኩራራት ሳይሆን የምስጋና ልብ የሚሆነው። በመገኘቱ ውስጥ እየተለማመድነው ያለነውን ሰላማችንን እንኳን እኛም ጭምር የማንረዳበት ጊዜ አለ። በስጦታ መገኘቱ ያገኘነው ሰላም አእምሮን የሚያልፍ ያሰኘው ሰዋዊ ማብራሪያ ስለሌለው ነው። ሰላሙ ከሰላም አለቃ “እንካችሁ” የምንባለው መለኮታዊ ስጦታ ነው።
አእምሮን የሚያልፍ ሰላም የጌታን ንግግር ያስታውሰናል፤ ሰላሙም የጌታ ሰላም ነው። የሚሰጠንም እርሱ ነው። ሰላሙም ዓለም የሚሰጠው ዓይነት አይደለም። መለያውና ምንጩም ዘላቂነቱ ነው። የተፈጻሚነቱ ዋስትና ራሱ እግዚአብሔር ነው። በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ አይደለምና አይናወጥም። በማግኘትና በማጣት ውስጥ አይነቀነቅም። የሚገኘውም ሁሉን ነገር ለእርሱ አሳልፎ በመስጠት ውስጥ ነው።
ልባችንና ሃሳባችን በነውጦች መካከል እንዳይበታተን የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የእርሱ ቅርበትና አብሮነት ነው። አብሮነቱ ልባችንንና ሃሳባችንን ለየቅል የሚያሮጥ አይደለም። አንዳንዴ እንደምንሆነው ሃሳባችንን አሸንፎ ልባችን ግን የሚሸነፍበት አይደለም። ልባችንና ሃሳባችን በስምረት በመገኘቱ ስለሚደገፍ አይናወጥም። ይህም በነውጥ ዓለም በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ ተስፋን እንድናደርግ ያስችለናል። ሦስተኛው መንገድ በእርግጥም የአምላክን ቅርብነት የማወቅ፣ የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ የማሳወቅ፣ ሰላምን ከሰላም አለቃ እንደ መለኮታዊ ስጦታ የመቀበል መንገድ ነው። አዲሱ ዓመትም የእግዚአብሔርን ቅርብነት የምናስታውስበትና በመገኘቱ የምንኖርበት ዓመት እንዲሆን ምኞቴም ጸሎቴም ነው።